የብሎግ ዝርዝር መረጃ

የማዕድን ልማት እና የወርቅ ምርት አፈጻጸም

ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አገራችን ካሏት ከፍተኛ የማዕድን ሀብቶች በተለይም የወርቅ ክማችት መካከል ዋነኛው በመሆኑ፣ ይህንን ተፈጥሯዊ ጸጋ ለክልሉ ሕዝብና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ በላቀ ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለፉት አምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች ተወስደዋል። ዘርፉ ከዚህ ቀደም ይገለጽበት የነበረውን ህገ-ወጥነት፣ ኮንትሮባንድ፣ ያለአግባብ ቁፋሮና የጥቁር ገበያ አሠራር በመቀየር ወደ ህጋዊ፣ የተቆጣጠረና ግልጽ የአሠራር መስመር የማስገባት ሥራ ተከናውኗል።

የክልሉ መንግሥት ከፌደራል ተቋማትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ጥብቅ የህግ ማስከበርና የቁጥጥር ሥራ፣ በባህላዊና በዘመናዊ አምራቾች የሚመረተውን ወርቅ ሙሉ በሙሉ ወደ ህጋዊ የገበያ ሥርዓት እንዲገባ ተደርጓል። በተወሰዱት የተቋማዊ አሠራር ማሻሻያዎች፣ የፍቃድ አሰጣጥና የቁጥጥር ሥርዓቶች ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በአስደናቂ ሁኔታ እንዲጨምር አስችሏል።

በዚህም መሠረት በ2017 በጀት ዓመት ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ የነበረውን 1,500 ኪ.ግ በእጅጉ በመብለጥ 4,767.9 ኪ.ግ ወርቅ ገቢ ማድረግ ተችሎ የነበረ ሲሆን፣ በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ የቁጥጥርና የህጋዊ አሠራር ሥርዓቱን በበለጠ በማጠናከር፣ ገቢ የተደረገው የወርቅ መጠን ወደ 8,961 ኪ.ግ (ከ89 ኩንታል በላይ) ማደግ ችሏል።

ይህ የተመዘገበው የወርቅ ምርትና ገቢ ዕድገት አገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚገጥማትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ አገራዊ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን፣ በክልሉ ለሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና ባህላዊ አምራቾች ህጋዊና ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ሚናው የጎላ ነበረ።

← ወደ መነሻ ተመለስ