የብሎግ ዝርዝር መረጃ

የመልካም አስተዳደር፣ ዲጂታላይዜሽን (መሶብ) እና ተቋማዊ ሪፎርም

ፖለቲካዊ ዘርፍ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት የሕዝብን እርካታ የሚያረጋግጥ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ከብልሹ አሠራር የጸዳ የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት አበይት የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም መሠረት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሰፊ የዲጂታላይዜሽን እና የተቋማዊ አሠራር ለውጥ ተተግብሯል።

በዚህ የሪፎርም እንቅስቃሴ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት (Mesob One-Stop Center) ሲሆን፣ በአሶሳ እና በቤጉ ከተሞች ዘመናዊ ማዕከላት ተገንብተው ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል። በእነዚህ ማዕከላት አማካኝነት ከ83 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ንክኪ ነፃ በሆነ (Fully Digitalized/Automated) አሠራር ለሕዝብ ክፍት ሆነዋል። ይህም አሠራር አገልግሎት ፈላጊዎች የሚያጋጥሟቸውን እንግልቶች፣ አላስፈላጊ ወጪዎችና ህገ-ወጥ አሰራሮችን በእጅጉ ያስቀረ ሲሆን፣ የዜጎችን እምነትና እርካታ ማሳደግ ችሏል

ከዲጂታላይዜሽን ሪፎርሙ ጎን ለጎን፣ የዜጎችን መረጃ ለማዘመንና ለዘመናዊ አሠራር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ለ330,000 (ሦስት መቶ ሠላሳ ሺህ) በላይ የክልሉ ነዋሪዎች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ ID) ምዝገባ ተካሂዶ መታወቂያ ተሰጥቷል። በተጨማሪም የወጣቶችን የዲጂታል ክህሎት ለማሳደግና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተከናወነው አገራዊ ንቅናቄ 26,714 ወጣቶች በ5 ሚሊዮን ኮደርስ ፕሮግራም አማካኝነት ስልጠናቸውን አጠናቀዋል።

ተቋማዊ ግንባታና የሕግ አውጪነትን በተመለከተ፣ የክልሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በርካታ አዋጆችና ደንቦችን መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን፣ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ላይም ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር (Oversight) ሥራዎችን አከናውኗል። የዚሁ ሪፎርም አካል የሆነው 7ኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ በክልሉ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተጠናቆ፣ አዲስ መንግሥት ለማቋቋምና ቀጣይነት ያለው የልማት ጉዞን ለማስቀጠል የሚያስችል ሙሉ ተቋማዊ ዝግጅት ተጠናቋል።

← ወደ መነሻ ተመለስ