የሰላም፣ ደኅንነትና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ አፈጻጸም

የሰላም፣ ደኅንነትና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ አፈጻጸም

ፍትህና መልካም አስተዳደር ዘርፍ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ከተከናወኑ በርካታ ተግባራት መካከል ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ የሁሉም ልማቶችና አገራዊ ዕድገቶች መሠረት ሆኖ ተወስዷል። ክልሉ የነበረበትን ውስብስብ የደኅንነት ሥጋት በመረደታ እና ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ በማመን፣ የክልሉ መንግሥት የሰላም በሮችን ሙሉ በሙሉ ክፍት በማድረግ ሰፊ የውይይትና የድርድር ስትራቴጂዎችን ተግብሯል።

በዚሁ መሠረት በክልሉ ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ታጣቂ ኃይሎች ጋር የተሳኩ የሰላም ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን፣ በተለይም ከቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) እና ከጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ጋር ታሪካዊ የሆኑ የሰላም ስምምነቶች ተፈራርመዋል። በእነዚህ የሰላም ስምምነቶች መሠረት የድርጅቶቹ አመራሮችና አባላት ትጥቃቸውን ፈተው በምህረት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የተደረገ ሲሆን፣ የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያንፀባርቁበት፣ በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴዎችም በባለቤትነት የሚሳተፉበት አስተማማኝ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የቦታው ታጣቂ ቡድኖችም የሰላሙን ጥሪ ተቀብለው ትጥቅ በመፍታት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ተደርጓል።

እነዚህ አበይት የሰላም ስምምነቶችና የተቀናጁ የሕግ ማስከበር ሥራዎች በክልሉ አስተማማኝ መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በዚህም ሂደት በክልሉ ተለይተው ከነበሩት 156 የጋራ ሥጋት ቀጠናዎች ውስጥ 130 የሚሆኑት (83.3 በመቶ) ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላማዊ ቀጠናነት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል

በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ የተመዘገቡት እነዚህ ስኬቶች ክልሉ ወደ መደበኛ የልማት፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እድገት ምዕራፍ እንዲሸጋገር አስተማማኝ መሠረት ጥለዋል።

በፍትሕና የሕግ ማስከበር ዘርፍ፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማስከበር ተቋማዊ ሪፎርሞች ተተግብረዋል። የፍትሕ አካላትን የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ግልጽ ለማድረግ፣ የዓቃቤ ሕግና የፍርድ ቤቶችን አሠራር በዲጂታል ሥርዓት የመደገፍ ሥራ ተጀምሯል። ከዚህ በተጨማሪ በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስና የጸጥታ መዋቅሮችን አቅም በመገንባት፣ የሙስና እና የህገ-ወጥ ድርጊቶች የመከላከል ሥራዎች በትኩረት ተከናውነዋል።

← ወደ መነሻ ተመለስ